ማህደርና ዳንሷ
ማህደር አሰፋ
አሰፋ ደመላሽና ርብቃ ፈይሳ ሽሮ ሜዳ በሚኖሩበት ጊዜ ነበረ ማሂ የተወለደችው። ነገር ግን አምስት አመት ሲሞላት ቤተሰቡ በሙሉ ወደ ቄራ ገቡ። ስለዚህ ማህደር የቄራ ልጅ ናት ብንል ይሻላል።
የኢትዬጵያ ቤተሰብ መቼም ሁሉም ልጅ ትምህርት ጎበዝ እንዲሆን እንደውም አንደኛ እንዲወጣ ነው ሚፈልገው። የጎረቤቴ ልጆች ሁለቱም ሶስተኛ ክፍል ናቸው መንታ ስለሆኑ ታድያ አባታቸው ሁለቱም አንደኛ እንዲወጡ ይፈልጋል። በመልክ ቢመሳሰሉም እንኳን እኮ ከሚፈተኗቸው ሰባት ወይም ስምንት ትምህርት ውስጥ ሁሉን አንድ አይነት መልሰው የአንድ ጥያቄ መልስ መለያየት እኮ አንደኛና ሁለተኛ ያደርጋቸዋል። ይህንን ለአባትየው ማስረዳት የልጅ አስተዳደጉን እንደ መውቀስ ስለሚቆጥረው አስተያየት መስጠትም ችግር ነው።
የማህደር አባትም ልጁ በትምህርት እንድትጎብዝ ምኞቱ ነው። ለትምህርት ዋናው ጠንቅ ደግሞ መዝናኛ ነው። እንደ አባት ልጁ መዝናናት ቀንሳ ትምህርቷ ላይ እንድታተኩር ግፊት ያደርጋል። ከቢሮ ዘበኛችን ጋር የሆነ ቀን ስናወራ ምን አሉኝ መሰላቹ ‘ሰው እኮ መዝናናት ያበዛው በምን መሰለሽ ልጄ በማዝናናት የሚተዳደረው ስለበዛ ነው’ አሉኝ። እንዴት ብዬ ጠየኳቸው ፈገግ ብዬና ለመልሳቸው ጓጉቼ። ‘ በመዝፈን፣ በመተወን፣ በመደነስ፣ መሳሪያ በመጫወት፣ መሳሪያ በማከራየት፣ በመሸጥ፣ ሚተዳደር ሲበዛ ማለቴ ነው’ ሲሉኝ በአስተሳሰባቸው ተገርሜ ነበረ። ‘መዝናናት ሲበዛ ኀገር ትሰንፋለች’ ብለውኝም ነበር።
የማሂ አባትም ሆነ እናት ልጃቸውን በጥሩ ሁኔታ አሳድገው የራሷን፣ የነርሱን አንዲሁም የሀገር ስም እንድታስጠራ ምኞታቸው ነበረ። ስለዚህ ማህደር አፄ ዘርዓይ ያዕቆብ ትምህርት ቤት ስትማር ጭምትና ዓይን አፋር ስለነበረች የዳንስ ግሩኘ አንዳላት አያውቁምም አይጠረጥሩምም ነበር። ይህንን ቢያውቁ ያለጥርጥር ያስቆማት እንደነበረ ስለምታውቅ ሁሉን ደብቃ በትምህርት ቤቱ ሚኒ ሚዲያ መሳተፍም ከግሩፗ ጋር መደነሱንም ቀጠለችበት።
አንድ ቀን እናቷ በቲቪ የሚያዩትን አላመኑም የገዛ ቆንጅዬ ልጃቸው ከአምስት ጓደኞቿ ጋር መድረኩን በዳንስ ተቆጣጥረውታል። መቼም ከዛ በኋላ መመለስ እንደሌለ ሳይገባቸው አልቀረም። ምክንያቱም የቤተሰብም ሆነ የሀገርን ስም የሚያስጠራ ልጅ የሚወደውንና ጎበዝ ነኝ የሚልበትን ማንኛውም ተሰጥዖ ትምህርትንም ጨምሮ በነፃነት እንዲከውን እንደወላጅ ደሞ መንገዱን እንዳይስት ካደረግን የምንመካበት ልጅ ይኖረናል።
ማሂ ትምህርቷንም እስከ ኮሌጅ በመማርም ትምህርት የተሰጥዖ ማበልፀጊያ፣ የአዕምሮ መግብ፣ የማገናዘብ ስጦታ እንደሆነ በስኬቶቿ አሳይታለች።
Comments
Post a Comment